ሚያዝያ 30 ቀን 2018 ዓ.ም
የኬንያ ከፍተኛ ወታደራዊ ልዑክ በመከላከያ ሠራዊት ፋውንዴሽን አዳማ ጋርመንት ኢንዱስትሪ ጉብኝት አደረጉ
በብርጋዲየር ጄኔራል ኦስካር ሙልይ የተመራው የኬንያ መከላከያ ኢንዱስትሪ ከፍተኛ ወታደራዊ ልዑክ፣ በመከላከያ ሠራዊት ፋውንዴሽን ስር የሚገኘውን የአዳማ ጋርመንት ኢንዱስትሪን የሥራ እንቅስቃሴ ጎብኝቷል። የኢንዱስትሪው ዋና ሥራ አስኪያጅ ሻለቃ ደሱ አብዲሳ ለልዑካን ቡድኑ ባደረጉት ገለጻ፣ ፋብሪካው ለሠራዊቱ የሚያስፈልጉ አልባሳትን በጥራትና በብዛት በማምረት ረገድ ያለውን አቅም አብራርተዋል። አክለውም ኢንዱስትሪው ቀደም ሲል ከውጭ ይገቡ የነበሩ ምርቶችን በሀገር ውስጥ በመተካት የሀገርን የውጭ ምንዛሬ እያዳነ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
የመከላከያ ሠራዊት ፋውንዴሽን ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ኮሎኔል አበበ አጥናፉ በበኩላቸው፣ ኬንያ ይህንን ጉብኝት ለማድረግ የኢትዮጵያን መከላከያ ሠራዊት ፋውንዴሽን አዳማ ጋርመንት ኢንዱስትሪ መምረጧ፣ በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን የቆየ ዲፕሎማሲያዊና ወንድማማችነት ግንኙነት የሚያሳይ መሆኑን ገልጸዋል።
የልዑካን ቡድኑ መሪ ብርጋዲየር ጄኔራል ኦስካር ሙልይ በበኩላቸው፣ ኢትዮጵያና ኬንያ በታሪክና በባህል እጅግ የተቀራረቡ መሆናቸውን ጠቅሰው፤ “ያለንን ወታደራዊ የኢንዱስትሪ ልምድ ለማጋራት ዝግጁ ነን” ብለዋል። ልዑካን ቡድኑም በተደረገላቸው አቀባበልና ገለፃ መደሰታቸውን ገልጸው፣ ለመከላከያ ሠራዊት ፋውንዴሽን አዳማ ጋርመንት ኢንዱስትሪ ከፍተኛ አመራሮች ምስጋና አቅርበዋል።
በጉብኝቱ ማጠናቀቂያ ላይ ብርጋዲየር ጄኔራሉ የሀገራቸውን አርማ የያዘ ልዩ ስጦታ ለመከላከያ ሠራዊት ፋውንዴሽን አዳማ ጋርመንት ኢንዱስትሪ አመራሮች አበርክተዋል።

