በመከላከያ ትምህርት እና ስልጠና ዋና መመሪያ ሎጀስቲክስ ኮሌጅ የአጭር ኮርስ ሰልጣኞች እና የመከላከያ ስታፍ ኮሌጅ የዲግሪ አንደኛ ዓመት ተማሪዎች በመከላከያ ሰራዊት ፋውንዴሽን አዳማ ጋርመንት ኢንደስትሪ ጎበኙ።
በጉብኝቱ ወቅት የአዳማ ጋርመንት ኢንደስትሪ ዋና ስራ አስኪያጅ ሻለቃ ደሱ አብዲሳ ለሰልጣኞቹ የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል። ዋና ስራ አስኪያጁ ስለ አጠቃላይ የኢንደስትሪው የስራ እንቅስቃሴ ሰፊ ማብራሪያ የሰጡ ሲሆን፣ ተቋሙ እየተጠቀመባቸው ያሉት ዘመናዊ የልብስ ስፌት ቴክኖሎጂዎች ለሠራዊቱ ጥራቱን የጠበቀ አልባሳት በተገቢው ፍጥነት ለማድረስና የሠራዊቱን የንብረት አቅርቦት ፍላጎት በአስተማማኝ ሁኔታ ለመሙላት የሚጫወቱትን ከፍተኛ ጥቅም በዝርዝር አስረድተዋል። ከጎብኚዎቹ ለተነሱ ጥያቄዎችም ማብራሪያ ሰጥተዋል።
የኢንደስትሪው ምክትል ስራ አስኪያጅ ኦፕሬሽናል መቶ አለቃ ሁንዱማ ዱሬሳ በበኩላቸው፥ ተቋሙ በልብስ ስፌትና ጋርመንት ዘርፍ በአሁኑ ወቅት የደረሰበትን ከፍተኛ የዕድገት ደረጃ ለጎብኚዎቹ አስረድተዋል። አክለውም ቀደም ሲል ከውጭ ሀገር ከፍተኛ ወጪ እየተደረገባቸው ይገቡ የነበሩ ወታደራዊና የተለያዩ አልባሳትን በአሁኑ ወቅት በሀገር ውስጥ የልብስ ስፌት ምርት መተካት መቻሉን በኩራት ገልጸዋል።
ልብስ ስፌት ፋብሪካ ቁጥር ኃላፊ መቶ አለቃ ጎሳ ንጉሴ እንደገለጹት፥ ተቋሙ ዘመናዊና የዘመኑን የልብስ ስፌት ማሽኖችና ቴክኖሎጂዎች ስራ ላይ በማዋል የምርት ጥራትንና የዕለታዊ ስፌት ፍጥነትን በከፍተኛ ደረጃ ማሳደግ ችሏል። ያለ ምንም ማቋረጥ (እረፍት) በከፍተኛ ቁርጠኝነት በመስራት ውጤታማ እየሆነ መምጣቱን እንዲሁም ይህንን የቴክኖሎጂ አቅም በመጠቀም ተቋማዊ የጋርመንት አቅሙን በከፍተኛ ደረጃ እያሳደገ መሆኑን አብራርተዋል።
ከጎብኚዎቹ መካከል የአጭር ኮርስ ሰልጣኝ የሆኑት ሻለቃ መሀመድ ኡመር እና የመከላከያ ስታፍ ኮሌጅ የዲግሪ አንደኛ ዓመት ተማሪ የሆኑት ሻምበል መከዳ ብርሃኑ በአዳማ ጋርመንት ኢንደስትሪ ባደረጉት ጉብኝትና በተመለከቱት የልብስ ስፌት የስራ ሂደት እጅግ መደሰታቸውን ገልጸው፤ ከተቋሙ ትልቅና ጠቃሚ የስራ ልምድ ማግኘታቸውን በደስታ ተናግረዋል።



