በኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ፋውንዴሽን አዳማ ጋርመንት ኢንዱስትሪ ሃምሌ 25 ቀን 2018 ዓ.ም
የመከላከያ ሰራዊት ፋውንዴሽን የቤቶች ልማት ዘርፍ በጋሻ መኖሪያ ቤቶች ፕሮጀክት ላይ ለላቀ አፈጻጸም አስተዋፅኦ ላበረከቱ አመራሮችና ሠራተኞች የምስጋናና የዕውቅና መርሃ ግብር አካሂዷል።
በፕሮግራሙ ላይ በክብር እንግድነት የተገኙት የመከላከያ የሰው ሀብት አመራር ዋና መምሪያ ሃላፊና የፋውንዴሽኑ የቦርድ አመራር ሌተናል ጀነራል አጫሉ ሸለመ፣ ፋውንዴሽኑ በአጭር ጊዜ ውስጥ ያስመዘገበው የግንባታ ዕድገት አበረታች መሆኑን ገልጸው፣ ይህም በቀጣይ የበለጠ ውጤታማ ሥራዎችን ለማከናወን ጠንካራ መሠረት እንደሚሆን አስታውቀዋል።
ፋውንዴሽኑ ከቤቶች ግንባታ ባሻገር በፋብሪካ፣ በጋርመንት፣ በፋይናንስና በሌሎች የልማት ዘርፎች በመሰማራት ራሱን ወደ ትልቅ ተቋም እየቀየረ መሆኑን ጠቅሰው፣ በፕሮጀክት አፈጻጸም ያስመዘገበው መሻሻል አስደናቂ ለውጥ ማምጣቱን አድንቀዋል። ይህም በአመራሩ፣ በባለሙያዎችና በሠራተኞች የተቀናጀ ጥረት የተገኘ ውጤት መሆኑን አስረድተዋል።
ዘመናዊ ቴክኖሎጂን በመጠቀም ለሠራዊቱ ምቹና ደረጃውን የጠበቀ መኖሪያ ቤት መገንባት ለሀገሪቱ አርአያ የሚሆን ተግባር መሆኑን ገልጸው፣ የተገኘው ስኬት የጋራ ሥራ፣ የቁርጠኝነትና የእኔነት ስሜት ፍሬ መሆኑን አስገንዝበዋል።
ሠራዊቱ በዋና ተልዕኮው ላይ በሙሉ እንዲያተኩር ፋውንዴሽኑ የመኖሪያ ቤቶች ግንባታን አጠናክሮ እንዲቀጥል አሳስበዋል።
የመከላከያ ሰራዊት ፋውንዴሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሜጀር ጀነራል ደረጄ መገርሳ በበኩላቸው፣ የተመዘገበው ስኬት በእኔነት ስሜት፣ በቅንጅትና በተቀናጀ ጥረት የተገኘ ውጤት መሆኑን ተናግረዋል።
የጋሻ ፕሮጀክት እየተገነባ የሚገኘው ዘመናዊ የመኖሪያ አፓርታማ ለሠራዊቱ ተነሳሽነት የሚፈጥርና ዓለም አቀፍ ደረጃን የጠበቀ ግንባታ መሆኑን ጠቅሰው፣ የ2018 ዓ.ም ዕቅድ በተሳካ ሁኔታ መጠናቀቁንና ለቀጣዩ የበጀት ዓመት አዳዲስ ፕሮጀክቶችን ለመጀመር ዝግጅት መጀመሩን ገልጸዋል።
በመከላከያ ፋውንዴሽን የቤቶች ልማት ዘርፍ ሀላፊ ኮሎኔል ታደሰ ጌታቸው እና የጋሻ ፕሮጀክት ኃላፊ ሌተናል ኮሎኔል ብርሀን ዘሙ በበኩላቸው፣ በዘመናዊ የግንባታ ቴክኖሎጂዎች እየተገነባ የሚገኘው ፕሮጀክት በተያዘለት የጊዜ ሰሌዳ መሠረት ተጠናቆ ለባለዕድለኞች ለማስረከብ በሙሉ አቅም እየተሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
አጠቃላይ የፕሮጀክቱ አፈጻጸም 75 በመቶ መድረሱን የተጠቀሰ ሲሆን 1 ሺህ 24 መኖሪያ ቤቶችን ለመገንባት ታቅዶ የነበረው ፕሮጀክት በዲዛይን ማሻሻያ 1,028 መኖሪያ ቤቶችን እንዲያካትት መደረጉን ገልጸዋል።
በመርሃ ግብሩም ለፕሮጀክቱ ስኬት የላቀ አስተዋፅኦ ላበረከቱ አመራሮችና ሠራተኞች የዕውቅና እና የምስጋና ሽልማት ተሰጥቷቸዋል።



