የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ክቡር ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ በመከላከያ ፋውንዴሽን ስር በሚገኙ ተቋማት ያደረጉት የስራ ጉብኝትና የሰጡት አቅጣጫ በድርጅቶቹ ውስጥ ከፍተኛ ተነሳሽነት በመፍጠር ለቀጣይ የስራ አፈፃፀም ጠንካራ ውጤት ለማስመዝገብ መነሳሻ መሆኑን የአዳማ ጋርመንት ኢንዱስትሪ የስራ ኃላፊዎች ተናገሩ።
የቴክስታይልና ጋርመንት ዘርፍ ኃላፊ ኮሎኔል አበበ አጥናፉ ፣ የአዳማ ጋርመንት ኢንዱስትሪ ሥራ አስኪያጅ ሻለቃ ኢንጅነር ደሱ አብዲሳ እና ምክትል ሥራ አስኪያጅ መቶ አለቃ ሁንዱማ ደሬሳ፣ ከ40 ዓመታት በላይ ታሪክ ያለውን ተቋም ከነበረበት መቀዛቀዝ በማውጣት ወደ ትርፋማነት ለማሸጋገር የሰራዊቱ ከፍተኛ አመራሮች ያደረጉት ያልተቋረጠ ክትትል፣ የሰጡት ድጋፍና የአመራር አቅጣጫ ወሳኝ ሚና ተጫውቷል ብለዋል።
እንደ ሀላፊዎቹ ገለፃ፣ ፋብሪካው ለሠራዊቱ የሚያስፈልጉ ዩኒፎርሞችና ሌሎች ቁሳቁሶችን ከማምረት ባለፈ፣ ለፌዴራልና ለክልል የፀጥታ ተቋማት እንዲሁም ለጎረቤት ሀገራት የጋርመንት ምርቶችን በማቅረብ ከፍተኛ አስተዋፅኦ እያበረከተና አቅሙንም እያጠናከረ ይገኛል።
በተቋሙ የሰራተኞችን አቅም ለማጎልበት ተከታታይ ስልጠናዎች መሰጠታቸው፣ ሥራን በእውቀት፣ በተጠያቂነትና በባለቤትነት ስሜት መፈፀማቸው ለውጤታማነታቸው መሠረት መሆኑንም ገልጸዋል።
ለማህበረሰቡ የሚሆኑ የጋርመንት ምርቶችን በተለያዩ የስርጭት አማራጮች ተደራሽ ለማድረግ እየሠሩ መሆናቸውን ጠቁመዋል።
ሀላፊዎቹ የ2019 የበጀት ዓመት ዕቅዶቻቸውን ከግብ ለማድረስና የላቀ ውጤት ለማስመዝገብ በትኩረት እየሠሩ መሆኑንም ገልጸዋል።
ከ40 ዓመታት በላይ ታሪክ ያለው የአዳማ ጋርመንት ኢንዱስትሪ በአምስት ፋብሪካዎች አማካኝነት ወታደራዊ ዩኒፎርሞችንና ሌሎች አልባሳትን በማምረት ለሀገር ውስጥና ለውጭ ገበያ የሚያቀርብ ሲሆን፣ ከሁለት ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የስራ ዕድልም ፈጥሯል።
በመከላከያ ፋውንዴሽን ስር የሚገኘው የጋሻ የመኖሪያ ቤቶች ፕሮጀክት ለመከላከያ ሠራዊት አባላት ዓለም አቀፍ ደረጃቸውን የጠበቁ የጋራ የመኖሪያ ቤቶችን በአዲስ አበባና በተለያዩ የክልል ከተሞች እየገነባ ሲሆን፣ የመከላከያ ባጅና ሜዳልያ ማምረቻ ድርጅትም ለሠራዊቱና ለሌሎች ተቋማት ደረጃቸውን የጠበቁ ምርቶችን በማምረት ላይ ይገኛል።




