የፌዴራል ማረሚያ ቤቶች ኮሚሽን ከፍተኛ ጥበቃ ማረሚያ ማዕከል ልዑክ በአዳማ ጋርመንት ኢንዱስትሪ የልምድ ልውውጥ ጉብኝት አደረገ
የፌዴራል ማረሚያ ቤቶች ኮሚሽን ከፍተኛ ጥበቃ ማረሚያ ማዕከል ልዑክ በመከላከያ ሰራዊት ፋውንዴሽን ስር በሚተዳደረው የአዳማ ጋርመንት ኢንዱስትሪ የስራ ጉብኝት አድርጓል።
በፌዴራል ማረሚያ ቤቶች የጋርመንት ኃላፊ በዋና ሳጅን ታሪኩ ጋዲሳ የተመራው ይህ ልዑክ፥ በኢንዱስትሪው ዘርፍ ያለውን ግንኙነት ለማጠናከርና የልምድ ልውውጥ ለማድረግ ያለመ መሆኑ ተገልጿል። ዋና ሳጅን ታሪኩ በወቅቱ እንደተናገሩት፥ በኢንዱስትሪው ዘርፍ የሚደረጉ መሰል የልምድ ልውውጦች ለተቋማት ውጤታማነት እጅግ አስፈላጊ ናቸው።
ልዑኩ ወደ ጋርመንት ኢንዱስትሪው በደረሰበት ወቅት የአዳማ ጋርመንት ኢንዱስትሪ የኦፕሬሽናል ምክትል ስራ አስኪያጅ መቶ አለቃ ሁንዱማ ዱሬሳ አቀባበል አድርገውላቸዋል። መቶ አለቃ ሁንዱማ ስለ ማኑፋክቸሪንግ ማዕከሉ አጠቃላይ የስራ እንቅስቃሴና ስኬቶች ለጎብኚዎቹ ሰፊ ገለጻ አድርገዋል።
ኢንዱስትሪው ዘመናዊ የልብስ ስፌት ማሽኖችን በከፍተኛ ደረጃ በማስገባት ስራዎችን እያከናወነ እንደሚገኝ የገለጹት ምክትል ስራ አስኪያጁ፥ ይህም የምርት ጥራትንና ፍጥነትን ከመጨመር ባሻገር ተወዳዳሪነትን እያሳደገ መሆኑን አስገንዝበዋል።
የፌዴራል ማረሚያ ቤቶች ኮሚሽን ልዑክ አባላትም በበኩላቸው በጉብኝቱ ያገኟቸው ተሞክሮዎች በማረሚያ ማዕከሉ ውስጥ የሚገኙ ታራሚዎችን በጋርመንት ሙያ በማሰልጠንና ወደ ማምረት ስራ በማሰማራት ረገድ ትልቅ እገዛ እንደሚኖራቸው ገልጸዋል።

